Ethiopic fonts
  Acrobat Reader
 


መዋቅር

የጃቫ ፕሮግራም የማያሻማ ፥ ግልጽ የሆነ መዋቅር አለው። መዋቅሩ መደብ/ክላስ ተብሎ በሚጠራ ነገር ላይ የተመሠረተ ነው። የጃቫ ፕሮግራም ያንድ ወይም ካንድ በላይ መደቦች ስብስብ ነው። ያለመደብ የሚጻፍ የጃቫ ፕሮግራም የለም። ስለሆነም ፕሮግራም ጸሐፊው መደብ ሲያውጅ፥ የመደብን መዋቅር በንጽህና የመከተል ግዳጅ አለበት። በደፈናው፥ የመደብ መዋቅር ይኸን ይመስላል፦

ምስል 2.1
1. class AdissClass
2.    {   
3.    }
 

ማሳሰቢያ፦ ተራ ቁጥር የተሰጠው ለማብራራት ይረዳ ዘንድ እንጂ ኮዱ ውስጥ መጨመር ስላለበት አይደለም። ስለዚህ ኮዱን ስንጽፍ፥ ተራ ቁጥሮችን መተው አለብን። በመጀመሪያ ይኸ ክላስ ምን እንደሚመስል በቅርብ እንመርምር።

  1. class የሚለው ቃል የጃቫ ተፈጥሯዊ ቃል ነው። መደብ ለማወጅ ወይም ለመፍጠር እንዲሁም የመደቡን ስም ለማውጣትና መዋቅሩን ለመዘርጋት እንጠቀምበታለን። በዚህ ምሳሌ መሠረት የመደቡ ስም AddisClass ሲሆን፥ መዋቅሩ ደግሞ በግራ ቅንፍ ዘለበት ({) ምልክት ተክፍቶ በቀኝ ቅንፍ ዘለበት (}) ምልክት ይዘጋል። class የሚለው ቃል በጃቫ የተሰጠው ልዩ ተግባር ይህ ስለሆነ፥ ለሌላ ስራ መጠቀም ወይም ተግባሩን መቀይር በፍጹም ክልክል ነው። ይኸና የመሳሰሉት ቃላት የተከለከሉ ቃላት ተብለው ይጠራሉ።
  2. ይህ ክላስ መዋቅር አለው እንላለን። ለምን? ያቀፋቸው ነገሮች ቅደም-ተከተል አላቸው፤ በተጨማሪ መጀመሪያውና መጨረሻው በግልጽ የተመለከተ ነው። ወደፊት እንደምናየው፥ መዋቅሩ እየሰፋና እየደመቀ ሲመጣ አስፈላጊነቱ እየዘለቀ ይመጣል።

ይህን ፕሮግራም በወግ ጽፈን፥ ኮምፓይል ብናደርገው፥ በደንብ ያልፋል። ማለትም የጃቫን ህግ ስላከበረ፥ ኮምፓይለሩ ወደ ሥራ የምናሠማራው ግልባጭ ፕሮግራም ይፈጥርልናል። ይሁን እንጂ ይኸን ፕሮግራም፥ ለሥራ እናሰማራህ ብንለው፥ ሁለት አበይት ችግሮች ይነሳሉ። 1ኛ) ይህ መደብ መጀመሪያና መጨረሻ ይኑሮው እንጂ በሰውነቱ ውስጥ ያቀፈው ምንም አይነት መመሪያ የለም። 2ኛ) የጃቫን ፕሮግራም ለሥራ ስናሰማራ፥ መነሻ ነጥብ ወይም መስመር ያስፈልገዋል። ይህ ምሳሌያችን ግን መነሻ ነጥብ ወይም መስመር ተነፍጎታል። በዚህ ምክንያት ወደሥራ ለማሰማራት ከሞከርን ውጡቱ ስህትት ሰርተሃል የሚል መልክት ይሆናል። በተግባር እናየው ዘንድ፥

  1. ከላይ የተሰጠውን ኮድ እናጻፍና ስሙ AddisClass.java የሚል ፋይል ውስጥ እንክተተው። (ማስታወሻ፦ ተራ ቁጥሮች የኮዱ አካሎች አይደሉም።)

  2. ኮዱን ኮምፓይል እናድርግ፦


    javac AddisClass.java

    ስህተቶች ካልተገኙ፥ የጃቫ ኮምፓይለር ሥራውን አጠናቆ በዝምታ ይመለሳል። ስሙ AddisClass.class የሆነ ፋይል ይፈጥራል። ለሥራ የምናሰማራው ይኸን ፋይል ወይም ፕሮግራም ነው።

  3. በመጨረሻ ፕሮግራማችን ለሥራ እናሰማራ፦

    java AddisClass

    (ማሳሰቢያ፦ ፕሮግራማችንን ለሥራ ስናሰማራ የፋይሉን ስም ተቀጥያ አንጨምርም።) የጃቫ ቨርችዋል ማሽን ወይም ጃቫ፥ ፕሮግራማችን ከመረመረ በኋላ፥ የሚከተለውን መልክት አውጥቶ ከሥራ ይወጣል።
    Exception in thread "main" java.lang.NoClassDefFoundError: AddisClass






smirmir@senamirmir.org
Copyright © 2001 Senamirmir Project