Ethiopic fonts
  Acrobat Reader
 


መላ ምታ

ምሳሌያችን የረባ ውጤት እንደማያመጣ ቀደም ብለን ተመልክተናል። ሁኔታውን ለማሻሻል፥ መውሰድ ካለብን እርምጃቸዎች መካከል አንዱ መላዎችን (methods/functions/operations) መጨመር ነው። መላዎች የመደብ ሠራተኞች ናቸው። ማንኛውንም ነገር የሚፈጽሙት/የሚያስፈጽሙት እነሱ ናቸው። መላዎች የሌሉት መደብ፥ ሠራተኞች የሌሉት ፋብሪካ ማለት ነው። መላዎች ሁልጊዜ የመደብ አባሎች ናቸው። በመደብ ሰውነት ውስጥ ይታቀፋሉ። የመደብ ንብረት ይሆናሉ። ይረዳ ዘንድ፥ አንድ መላ ክመደባችን ውስጥ እንጨምር።

ምስል 2.1
1. class AdissClass
2.    {   
3.    public static void main(String[] args)
4.       {
5.       System.out.println("Java in Amharic") ;
6.       }
7.    }
 

እንደ መደብ ሁሉ፥ ማንኛውም መላ፥ መጠሪያ ስምና የራሱ የሆነ ሰውነት አለው። በዚህ ምሳሌያችን የመላው ስም main ሲሆን፥ በግራ ቅንፍ ዘለበት ({) እና በቀኝ ቅንፍ ዘለበት (}) ምልክት ያለው ክፍል ደግሞ የመላው ሰውነት ነው። በ3ኛውና በ6ኛው መስመር መካከል ያለው። ምሳሌያችንን እንደገና በዝርዝር እንመልክት።

  • መስመር 1፦ ክላስ ያውጃል ወይም ይፈጥራል። የክላሱ ስም AdissClass ነው። class የሚለው ቃል የጃቫ ቋንቋ ለዚህ ተግባር ስለመደበው፥ ለሌሎች ተግባር መጠቀም ክልክል ነው። እንደዚህ አይነት ቃላት፥ የተከለከሉ ተብለው ይጠቀሳሉ።
  • መስመር 2፦ የክላሱ ሰውነት እዚህ ይከፈታል። { ምልክት ወይም ሆሄ፥ የግራ ቅንፍ ዘለበት (open curly brace) ተብሎ ይጠራል።
  • መስመር 3፦ ይህ መመሪያ መላ መቺ ነው። መላ ፈጣሪ። የመላው ስም main ነው። ከስሙ ጋር የተያያዙትን ነገሮች አሁን እዚህ አንነጋገርባቸውም። ነገር ግን ወደፊት በሰፊው እንመለስባቸዋለን። ይህ መላ ከሌሎች ሁሉ የሚለይበት አንድ ጠባይ አለው። እሱም የፕሮግራሙ የስራ መነሻነቱ ነው። ማለትም ፕሮግራሙን ለሥራ ስናሰማራ፥ ሥራውን የሚጀምረው ከዚህ መላ ነው። main የሚለውን ስም ላንድ መላ ከሰጠን፥ ፕሮግራሙ ሥራውን ከዛ እንዲጀምር ወስንን ማለት ነው። በሌላ አነጋገር ጃቫ main የሚል ስም ያለውን መላ ልዩ ቦታ ይሰጠዋል። ስለሆነም፥ main የተከለከለ ቃል ነው። ከተሰጠው ተግባር ውጪ መሰየም አይቻልም።
  • መስመር 4፦ የመላው ሰውነት እዚህ ይከፈታል። እያንዳንዱ መላ የራሱ መጀመሪያና መጨረሻ አለው። በመሆኑም፥ ይህ መላ ሰውነቱን እዚህ ይጀምራል።
  • መስመር 5፦ ይህ መመሪያ በሁለቱ ጥቅስ ምልክት ያሉትን የእንግሊዘኛ ሀረጎች ሞኒተሩ ላይ ይጽፋል።
  • መስመር 6፦ የመላው ሰውነት እዚህ ይዘጋል። ሥራውን ጨረሰ ማለት ነው።
  • መስመር 7፦ የክላሱ ሰውነት እዚህ ይዘጋል። የ} ምልክት ወይም ሆሄ፥ የቀኝ ቅንፍ ዘለበት (close curly brace) ተብሎ ይጠራል።
    • አሁን ይኸን ፕሮግራም በሥነ ሥርዓት ኮምፓይል አድርገን ለሥራ ብናሰማራው፥ ሞኒተሩ ላይ Java in Amharic የሚለውን ሀረግ ይጽፋል።







      smirmir@senamirmir.org
      Copyright © 2001 Senamirmir Project