Ethiopic fonts
  Acrobat Reader
 


መደብና ርባታ

ስለመደቦች ስንወያይ፥ አንድ መደብ ሌላውን እንዴት መጠቀም ይችላል የሚለውን ጥያቄ ሳናነሳ ብዙ ርቀን መሄድ አንችልም። በዝምታ ታለፈ እንጂ፥ ቀደም ብለን ያየነው ምሳሌያችን ሌሎች መደቦች ተጠቅሟል። በዚህ ክፍል፥ አንድ መደብ ሌላውን እንዴት እንደሚገለገል በትንሹ ከራሳችን ጋር እናስተዋውቃለን።

አንድ መደብ ሌላውን መገልገል ሲሻ፥ አብዛኛውን ጊዜ በቅድምያ መቃጣት ያለበት እርምጃ፥ ግልጋሎት እንዲሰጥ የተፈገውን መደብ ማራባት ነው። ለዚህ አብይ ምክንያቱ፥ በርባታ መንገድ የሚሠሩ መደቦች፥ ከፍተኛ ችግሮች መፍትሄ ለመስጠት አመቺ ስለሆኑ ነው። መደቦችን የማራባቱ ሂደት በእንግሊዘኛ instantiation ይባላል። የተራቡት ነገሮች፥ ባማርኛ ርቢ የምንላቸው፥ በእንግሊዘኛ objects ይባላሉ።

ርቢዎች/ኦብጀክቶች እንዴት ይፈጠራሉ? ከምን ይፈጠራሉ? ያፈጣጠራቸው ህግ ምንድን ነው? አጠቃቀማቸውስ? እነዚህን ጥያቆዎች ገርበብ ባለ መልስ እናያቸዋለን። በምሳሌ እንጀምር።

ምስል 2.1
1.    class Hissab
2.       {   
4.       void demir(int x, int y)
5.          {
6.          int result = 0 ;
7.          result = x + y ;
8.          System.out.println(result) ;
9.          }
10.      }
11.       
12.
13.   public class Temari
14.      {
15.       public static void main(String[] args)
16.         { 
17.         Hissab assila = new Hissab() ;
18.         assila.demir(13, 19) ;
19.         }
20.      }
 

ይህ ኮድ ሁለት መደቦች/ክላሶች አሉት፦ Temari እና Hissabሂሳብ ከተራ ቁጥር 1 እስከ 10 ያለው ሲሆን፥ ተማሪ ደግሞ ከተራ ቁጥር 13 እስከ 20 ያለው ነው። ኮዱን ፋይል ውስጥ ስንከት፥ የፋይሉ ስም Temari.java ሊሆን ይገባል።

አስቀድመን የተማሪን መደብ በጥሞና እንመልከት--ከተራ ቁጥር 13--20። በዚህ መደብ ውስጥ ያለን ነገር፥ main ተብሎ የሚጠራ መላ ብቻ ነው። የሜይን መላ ከሌሎች የሚለየው፥ ፕሮግራማችን ለሥራ ሲሰማራ፥ ተግባሩን የሚጀምረው ከሱ መሆኑን ከዚህ በፊት አንስተናል። በዚህ መላ (በሜይን ሰውነት) ስር ሁለት ቃለ-መመሪያዎች አሉ--ተረ ቁጥር 17 እና 18። እንዚህ ሁለት ቃለ-መመሪያዎች የዚህ ክፍል እንዝርት ናቸው።

ተራ ቁጥር 17 አዋጅ ነው--የሂሳብን መደብ እገለገላለሁ ይላል። በሌላ አነጋገር፥ የተማሪ መደብ ሂሳብን ለመጠቀም፥ ርቢውን መጀመሪያ ይፈጥራል። ርቢውን እንጂ፥ የሂሳብ መደብን በቁም መጠቀም ስለማይችል።

ከዚህ አባባል የምንረዳው፥ መደቦች/ክላሶች በተፈጥሯቸው ጥሬ-ዘር መሆናቸውን ነው። መደቦች ባምሳላቸው መራባት ይችላሉ፤ በሰውነታቸው ውስጥ ወይም በሌላ መደብ ሰውነት ውስጥ።

ስለሆነም፥ ራሳቸውን ለሪቢ ማዘጋጀት ማለተም ባምሳላቸው ነገሮች እንዲፈጠሩ መፍቀድ አንዱና ቀዳማዊ ተግባራቸው ነው። ምክንያቱም፥ መደቦች ግልጋሎታቸውን የሚሰጡት በርቢዎቻቸው በኩል ስለሆነ። ለዚህ ነው የተማሪ መደብ፥ ሂሳብን ለመገልገል ርቢውን መፍጠር የተገደደው። በነገራችን ላይ፥ ከዚህ ለየት ያለ ጠባይ ያላቸው የመደብ አይነቶች አሉ። ነገር ግን እዚህ እነሱን አንመለከትም።

ምስል 2.2
 

ምስል 2.2 የሚያሳየው የመደብን ያረባብ ዘይቤ ነው። በዚህ መንገድ ርቢ ይፈጠራል። ካንድ መደብ፥ አንድ ወይም ከዛ በላይ ርቢዎች መፍጠር እንችላለን። ከሆነ፥ እያንዳንዱ ርቢ የራሱን ሕልውና ይዞ ይሠራል፤ ይኖራል። በዚህ ምሳሌያችን ከሂሳብ መደብ የፈጠርነው አንድ ርቢ ነው። ስሙም አስላ ወይም assila

ምስል 2.3
 

አስላን በተራ ቁጥር 18 ላይ በግልጋሎት ላይ አውለናል። ምስል 2.3 ፍችውን፥ ዝርዝሩን ደግሞ ከዚህ በታች እናገኛለን።

  • assila፦ የርቢ ስም ሲሆን የተፈጠረው በሂሳብ አምሳል ነው።

  • . ፦ አባል አመልካች ነጥብ ነው። ከነጥቡ በኋላ የሚገቡ ነገሮች፥ የርቢው አባል መሆን አለባቸው። አስላ የሂሳብ መደብ ዘር ስለሆነ፥ በሂሳብ መደብ ስር ያሉትን አባለት ለመጥራት፥ ለማመልከት፥ ለማጣቀስ ወይም ለመደልደል፥ በስሙና ባባላቱ ስም መካከል ነጥብ ይጨምራል። ይህ የጃቫ ህግ ነው።

  • demir(13, 19)፥ ይህ ሀርግ ከነጥብ በኋላ የገባ ነው። ከላይ እንደተጠቀሰው፥ ከነጥብ በኋላ የሚገቡ ነገሮች ካባላት ጋር የተያያዙ ናቸው። በዚህ መሠረት፦ ይህ ሀረግ፥ ደምር ተብሎ የተሰየመው መላ ሁለቱን ቁጥሮች ተቀብሎ እንዲደምር ይጠይቃል። ደምር፥ መላ እንደመሆኑ መጠን፥ ይህ ጥሪ ሲደርሰው፥ የተላኩትን ሁለት ቁጥሮች ደምሮ፥ ውጤታቸውን ሞኒተር ላይ በመጻፍ ተልዕኮውን ያጠናቅቃል።






smirmir@senamirmir.org
Copyright © 2001 Senamirmir Project