XML Glossary









FAQ Sections
Introduction
XML Overview
XML FAQ
Glossary
Resources











  


ምእላደ ቃላት

You will find the PDF version here
ሃቴማላ (HTML)
ሃቴማላ፠ ፥ ሰነዶች በዌብ ገጽ ላይ እንዴት እንደሚቀመጡና መልካቸውስ ምን መምስል እንዳለበት መግለጫ መንገድ ነው። የዌብ ገጽ ስፋት ፥ የፊደላት አይነትና ቀለም ፥ ያርስቶችና ያንቀጾች አቀማመጥ ፥ ካንድ ነጥብ ወደሌላ መስፈንጠሪያ መንገዶችንና የመሳሰሉትን ይገልጻል። ባጭሩ፥ ሃቴማላ የገጽ መግለጫ ቋንቋ ነው።
ሆሄ ፥ ሆሄያት (ለብዙ) (character)

ማንኛውም ፊደል፥ የንባብ ምልክት፥ ሥርዓተ-ነጥብ፥ ቁጥር፥ ምልክት። ለምሳሌ፦ ሀ፥ ለ፥ ሐ፥ መ ... ፤ 1፥ 2፥ 3፥ ...።

ኅላፍ (left-margin)

ከግራ ጠርዝ እስከ ጽሑፍ መወደቂያ ያለው ክፍት ቦታ።

ኆኅት፥ ኆኅያት (ለብዙ) (white space)

በፊደላት፥ መካከል ያለ ክፍት ቦታ።

መሣሪያ (tool)
ፕሮግራም ጸሐፊዎች የተለያዩ መፍትሄዎች ለመገንባት የሚጠቀሟቸው ፕሮግራሞች። ለምሳሌ ንባብ መከተቢያ።
መረጃ፥ (ዴታ) (data)

ስለተካሄደ ወይም ስለተከናወነ ድርጊት ያልተበረዘ ቃል። ስለቦታ፥ ስለሰው ልጅ፥ ስለጠፈርና የመሳሰሉት ያልተበረዘ ቃል። የአፍሪካ የህዝብ ቁጥር፥ ዓመታዊ የኑሮ ገቢ፥ መልክአ-ምድርና የመሳሰሉት እርግጠኛ መረጃዎች ናቸው። የሰው ልጅ ስም፥ ዕድሜ፥ ቁመት፥ መኖሪያ ቦታና ሌሎችም እንደዚሁ መረጃዎች ናቸው። ባጠቃላይ መረጃ ማለት እውን ቃል ስለቦታ፥ ስለድሪጊት፥ ስለተፈጥሮ፥ ስለሰባዊነት እንዲሁም ሌሎች።

መቃኛ ፕሮግራም (browser)
ዌብ ገጾችን ለማንበብ ወይም ለማተም የኢንተርነት ተጠቃሚዎች የሚገለገሉት።
መነሻ ገጽ (home)
የማንኛውም ዌብ ገጽ የግንባር ክፍል፤ ገጹ ሲከፈት መጀመሪያ የሚመጣው እይታ።
ሜታዴታ (metadata)
ሜታዴታ ሲሉ ፥ ባጭሩ የመረጃዎች መረጃ ወይም የዴታዎች ዴታ ለማለት ነው።
መዋቅር (structure)
1ኛ ያካል አቋቋም፥ አወቃቀር ከላይ እስከ ታች። 2ኛ በዲስክ ላይ ወይም በሜሞሪ ውስጥ መረጃዎች ሲሰፍሩ የሚኖራቸው አሠፋፈር፥ አገነባብ። በኮምፕዩተር ሳይንስ ዓለም፥ የይዘቶች አጠነቃቀር በዛፍ ይመስላል። የዛፍ አቋቋም፥ ሥርን ፥ ግንድንና፥ ቅርንጫፎችን ይጨምራል። እንደ መሰላል ዛፍን መውጣትና መውረድ ይቻላል። ይዘቶችን በዛፍ አወቃቀር ማጠናቀሩ እጅግ ብዙ ጥቅሞች አሉት።
ሲ++ (C++)
በቢየርን ስተሮቭሰተሩፕ (Bjarne Stroustrup) እአአ በንጋቱ 1980 ላይ የተፈጠረ ፕሮግራም መጻፊያ ቋንቋ ነው። ባለፉት አያሌ ዓመታት፥ ሲ++ ከፍተኛ ተቀባይነትንና ዝናን ያተረፈ ቋንቋ ነው። የዓለም አቀፍ የስታንዳርድ ድርጅት የቋንቋው የበላይ ጠባቂ ሲሆን፥ ማንኛውም ሰው ያለምንም ጫናና ክፍያ ቋንቋውን ለተፈለገው ጉዳይ መጠቀም ይችላል።
ሰርቨር (server)
በኮምፕዩተር መረብ ውስጥ፥ ለተከታይ ኮምፕዩተሮች ልዩ ልዩ ግልጋሎት ሰጪ ኮምፕዩተር፤ አባወራ ኮምፕዩተር።
ሰነድ-አይነት-ደንጋጊ (ሰአደ) (DTD: Document Type Definition)
በኤማላ አዲስ የምልክት ቋንቋ መፍጠሪያ ፋይል ወይም ክፍል።
ሠንጠረዥ (table)

በረድፍና ባምድ የተሸነሸነ፤ ነገሮችን በጐንና በቁም ያሠለፈ፤ የጽሑፍና የሥዕል አቀማመጥ። ሠንዘረዥ በመስመር ሊታጠር ወይም ላይታጠር ይችላል።

ሲ/ኤስ/ኤስ (CSS)
የዓላም-አቀፍ-ዌብ ኮንሰርሽየም ሥራ ነው። ሃቴማላ (HTML) መስጠት የማይችለውን የጽሑፎችንና የሥእሎችን አቀማመጥና መልክ ማዘጋጂያ ፟ገጽ ገላጭ ቋንቋ፠።
ሥምሪት (run program)
ኮምፕዩተሮች ላይ ፕሮግራሞችን ለሥራ ማንቀሳቀስ፥ ማስነሳት፥ ማራመድ።
ስላሽ (slash)

የላቲን ሆሄ (/)

ሥርዓተ-ነጥብ (panctuation)

በሥርዓተ-ፊደል ውስጥ የሚገኙ የንባብ ምልክቶች፤ ለምሳሌ !፤፥ ። ፣ ፟ ፠

ሶፍትዌር (software)
ኮምፕዩተር ላይ ሥራዎችን ለማካሄድ የሚያስችሉ ፕሮግራሞች ካሠራር መመሪያዎች ጋር።
ስክ-ንባብ (string)

ካንድ በላይ ሆሄያት የያዘ። ቃል ወይም ኢቃል፥ ሐረግ ወይም ኢሐርግ፥ ዐርፍተ-ነገር ወይም ኢዐርፍተ-ነገር። ስክ-ንባብ የግድ ቃል፥ ሐረግ ወይም ዐርፍተ-ነገር እንዲሆን አይገደድም። ለምሳሌ፥ ሀሀሀሀ፥ ለለለለ፥ ሐሐሐሐ እና ሀለሐመ ስክ-ንባብ ናቸው።

ረድፍ (row)

በጐን የተደረደረ፥ የተሠለፈ፥ የተቀመጠ። በጋድም የተሰካካ፥ የተገጣጠመ።

ቃለ-ኆኅት (word separator)

ቃላት ለመለያየት የሚገባው ክፍት ቦታ። የሁለት ነጥብ እኩሌታ።

ቃለ-መመሪያ (statement)
ፕሮግራም ሲጻፍ የሚስነዘረው እያንዳንዱ መመሪያ።
ቃለ-ምልክት (tag)
1ኛ በኤማላ ሰነዶች ውስጥ ይዘቶቹን ገላጭ ፍሬ ቃላት፤ በ(<>) ምልክት የሚታጠሩት። በሃቴማላ ቃለ-ምልክቶች ፥ ተነባቢው ነገር እንዴት መቀመጥ/መታይት/መጻፍ/መደርደር እንዳለበት ለመቃኛ-ፕሮግራም እዝ የሚሰጡ 2ኛ ከፋች ቃለ-ምልክት (open tag)፦ እንደ <
ቃለ-አንቀጽ (XML entity)
ቃለ-አንቀጽ፦ አኅጽሮተ-ቃላትንና ቅጽል ስሞችን ይመሠርታል።
<!ENTITY aau "Addis Ababa University">
ቃለ-አዋጅ (declaration)
ፕሮግራም ሲጻፍ መረጃ/ዴታ መጠበቂያ የሜሞሪ ክፍል መክፈቻና መሰየሚያ ቃል።
ቃል (word)

አንድ ወይም ካንድ ፊደል በላይ የያዘ፥ ትርጉም ያለው።

ቀኝ ኧንግል ብራኬት (right angle bracket)

የላቲን ሆሄ (>)

ባለሰነድ-ሠራሽ (customize)
በኤማላ ሰነዶች አዘጋጆች የሚፈጠር ቃለ-ምልክትና የመሳሰለው።
ተመም (faq)
የኢንተርነት ውይይት መድረኮች ውስጥ ተመሳሳይ ጥያቄዎች በጣም ተደጋግመው ይቀርባሉ። በዚህ የተነሳ የሚፈጠረውን መጨናነቅ ለመቀነስ እንዲሁም የጠያቂዎችን ፍላጐት ለማርካት፥ ተደጋጋሚ መጠይቆችና መልሶቻቸው በተፈለገው ጉዳይ ይዘገጃሉ። እንደዚህ አይነት ጽሑፎች/ሰነዶች ተደጋጋሚ መጠይቆችና መልሶች (ተመም) ወይም በእንግሊዘኛ Frequently Asked Questions ይሏቸዋል።
ታብ (Tab)

የተመጠነ ክፍት ቦታ ፈጣሪ የኪቦርድ ኪ ወይም ሆሄ።

ተውላጠ-ቃል (variable)
ፕሮግራም ሲጻፍ መረጃ/ዴታ መጠበቂያ የሜሞሪ ክፍል፥ አይነት፥ መጠንና ስም ያለው።
ትልቁ/ትንሹ ሆሄ (ፊደል) (uppercase/lowercase letters)

በላቲን ሥርዓተ-ፊደል ውስጥ በሁለት መልክ የሚጻፉ ፊደላት አሉ። አነሱም ትልቁ ፊደል (uppercase/capital letters) እና ትንሹ ፊደል (lowercase/small letters) ናቸው። ትልቁ ፊደላት A, B, C,..., Z ሲሆኑ ፥ ትንሾቹ ፊደላት ደግሞ a, b, c, ..., z ናቸው።

ነጠላ-ጥቅስ-ምልክት (single quote)

ጥቅሶች መከለያ የላቲን ንባብ ምልክት ('')።

ንባብ (text)

ንጹሕ አንድ ወይም ካንድ በላይ ቃላትን የያዘ የወረቀት፥ የቃል ወይም ኤለክትሮኒካዊ ጽሑፍ።

አኀጸሮተ-ቃል (abbreviation)
አንድ ወይም ካንድ በላይ የሆኑ ቃላትን ባጭር ቃል መወከል ለጽሑፍ፥ ለንግግር። ዓለም አቀፍ ዌብ (ዓአዌ)፥ አዲስ አበባ (አአ)፥ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማኅበር (ኢተማ)፥ ወዘተ።
ዐረፍተ-ነግር (sentence)

በሰዋሰው ህግ መሠረት ታነጸው፥ ባራት ነጥብ የተደመደሙ ቃላት።

አንቀጽ (paragraph)

ካንድ በላይ ዐረፍተ-ነገሮችን የያዘ የገጽ ጽሑፍ።

አዲስ መስመር (new line)

1ኛ አዲስ አንቀጽ (paragraph) መጀመሪያ። 2ኛ መስመር አጣፊ ሆሄ/ሆሄያት።

አሳሽ ኢንጅን (search engine)
ኢንተርነት ውስጥ ሰነድ መፈለጊያ ዌብ ገጾች፥ እንድ www.google.com፥ www.altavista.com እና የመሳሰሉት።
አብይ-አንቀጽ (XML element)
አብይ-አንቀጽ፦ ያንድን ተናጠል ይዘት መጠሪያ፥ የይዘት አይነት፥ እንዲሁም በክልሉ መስፈር ያለባቸውን ሌሎች አንቀጾች ይመሠርታል። ለምሳሌ፦
<!ELEMENT periodic-table (element)+>
አገናኝ-ቃል (hyperlink)
የዌብ ገጽ ሰነዶች አስተሳሳሪ፥ አስተባባሪ፤ ከገጽ ወደ ገጽ አሸጋጋሪ። ይህ ቃል <a href="www.senamirmir.org">ስንምርምር ገጽ</a> ወደ ስነምርምር ገጽ መስፈንጠሪያ ነው።
ዓለም አቀፍ ዌብ ኮንሰርሽየም (W3C: World Wide Web Consortium)
በፍቃደኝነት ላይ የተመሠረተ፥ በዌብ ፋጣሪ ሊ በርነር-ሊ የሚመራ፥ የሃቴማላ (HTML)፥ የኤማላ (XML)፥ እና አያሌ ሌሎች ሥራዎች የበላይ ጠባቂ ድርጅት። የዓለም አቀፍ ዌብ ኮንሰርሽየም ገጽ http://www.w3.org ነው።
ኤማላ (XML)
የExtensible Markup Language አኅጽሮተ-ቃል። በተለምዶ XML የሚለው አኅጽሮተ-ቃል ባማርኛ ኤከስ/ኤም/ኤል ይሆናል። ይህን የመጨረሻ ቃል እንዲያጥር ቢደረግ ኤ/ክስምል ይመጣል። ሌላው አማራጭ ለራሱ ለExtensible Markup Language እኩሌታ ያማርኛ ትርጉም ማበጀት ነው። ተስፋፊ አካላይ ቋንቋ፤ ተስፋፊ አመላካች ቋንቋ፤ ወይም የተስፋፊ መቀነፊያ ቋንቋ፤ ለሙከራ ያህል ጥሩ ናቸው። በአኅጽሮተ-ቃል መልካቸው በተራ፦ ተ/አ/ቋ እና ተ/መ/ቋ ይመጣሉ። ስየማ ውስጥ አሁኑኑ ከመግባት፥ በኤማላ መርጋቱ ለጊዜው ያመቻል።
ዓምድ (colmn)

ገጽ ላይ በቁም የተሸነሸነው ንባብ። በቁም የተሸነሸነው የሠንጠረዥ አካል።

ዕሴት (value)
በተውላጠ-ቃለ ወይም በሜሞሪ ክፍል ውስጥ የሚጠበቅ ቁጥር፥ ሆሄ፥ ስክንባብ፤ ባጠቃላይ ዋጋ፥ መጠን፥ ተቆጣሪ ፥ ተተማኝ።
እይታ ፥ ገጽታ (screen)

ጹሑፎች፥ ግራፊክሶችና የመሳሰሉት የሚታዩበት የኮምፕዩተር ሞኒተር ክፍል፤ ፊት ለፊት ያለው።

ኮምፕዩተር መረብ (computer network)
በሽቦ፥ በስልክ፥ በሳተላይት እንዲሁም በልዩ ልዩ ሞገድ ተሳስረው ለመገናኛ የበቁ የኮምፕዩተሮች ስብስብ።
ዌብ ገጽ (web page)
በኢንተርነት የኤሌክትሮኒክ ሰነዶች፤ ንባብ፥ ግራፊክስ፥ ድምፅ እና ሌሎች ነገሮችን የሚይዙ። ለማንበብ ወይም ለማተም መቃኛ ፕሮግራም የሚጠይቁ፤ በሃቴማላ ቋንቋ የተዘጋጁ።
ዴታ አይነት (data type)

የቁጥር አይነቶች፦ ሙሉ ቁጥር (integer)፥ ፍሎት ቁጥር (float)፤ ሆሄ (character)፥ ቡሌን፥ እውነት (true)፥ ሐሰት (false)። ቁጥሮች በመጠን ማለትም በሚይዙት የሜሞሪ ስፋትና ጥበት ይከፈላሉ፥ ለምሳሌ፦ byte፥ short፥ int፥ long፥ float፥ double እና የመሳሰሉት።

ድርብ-ጥቅስ-ምልክት (double quote)

ጥቅሶች መከለያ የላቲን ንባብ ምልክት ("")።

የግል ኤመልክት መድረክ (mailing-list group)
በኤለክትሮኒክ መልክት ልውውጥ ላይ የተመሠረተ፥ ፍቃደኛ አባላትን ያቀፈ፥ መልክቶች ላባላት ብቻ የሚሠራጭበት፥ የራሱ የሆነ አስተዳዳሪ ያለው፥ የግድ የኢንተርነት ቁራኛ ያልሆነ፥ ከሁሉም በላይ ባንድ ዓላማ ላይ የተመሠረተ የግል ስብስብ ነው።
ዩንኮድ (Unicode)

1ኛ ፊደላትን ኮምፕዩተር ውስጥ ለማስገባት ወይም በመስመር ለመለዋወጥ፥ ፊደላቱ የማያሻማ ኮድ መሰየም አለባቸው። ኮምፕዩተሮች ፊደላቱን የሚለዩት በዛ ኮድ እንጂ በመልካቸው አይደለም። ኮዶቹ የሚሠሩት ከቁጥር ነው። አያሌ የኮድ ስልቶች በሥራ ላይ ውለዋል። በዚህ የተነሳ አለመግባባት፥ አለመጣጣም፥ ግጭት አለ። ዩኒኮድ አንድ ወጥ የሆነ ስልት ወይም ሠንጠረዥ ለመገንባት የሚሞክር መደበኛ ወይም ስታንዳርድ (standard) ነው። 2ኛ ዩኒኮድ መደበኛ (Unicode standard)፦ ለኮምፕዩተሮች ሥራ፥ የዓለም ቋንቋዎች ፊደላትን በኮድ የሚወክል ሠንጠረዥ፤ መደበኛ። 3ኛ ዩኒኮድ ኮንሰርሽየም (Unicode consortium)፦ በፍቃደኝነት ላይ የተመሠረተ፥ ፊደላትን ኮድ የሚሰይም ዓለም-አቀፋዊ (ዓለማቀፋዊ) ተቋም ነው። በዩኒኮድ መሠረት እያንዳንዱ ፊደል ሁለት ባይን የሜሞሪ ቦታ ይይዛል።

ዩዝነት (Usenet)
በዓለም አቀፍ ደረጃ፥ ኢንተርነት ላይ በፍቃደኛነት የተቋቋሙና የሚካሁዱ ኤመልክታዊ የውይይት መድረኮች። ቁጥራቸው ከ30,000 በላይ ይሆናል ተብሎ ይገመታል። ዩዝነት መድረኮች ኢንተርነት መግባት ለሚችል ሰው ሁሉ ክፍት ናቸው። ይዘታቸው ይፋ ነው። ዩዝነት መድረኮች ውስጥ በተናጋሪነት ወይም ባዳማጭነት ለመሳተፍ ልዩ ፕሮግራም ይጠይቃል።
ይዘት (content)
1ኛ በመያዣ ውስጥ የተቀመጠ ነገር። 2ኛ በፋይል ውስጥ የተቀመጠ ጹሑፍ፥ መረጃ፥ ዌብ ሰነድ፥ ቃላዊ-ሥዕል፥ ቃላዊ-ድምፅ፥ ወዘተ።
የጥቅስ ምልከት (quotation mark)

የኢትዮጵያ ፊደል የጥቅስ ምልከት (፟፠)።

ግልየት (right-margin)

ከቀኝ ጠርዝ እስከ ጽሑፍ መወደቂያ ያለው ክፍት ቦታ።

ዴታቤዝ (database)
በኮምፕዩተር ማዕከላዊ መረጃ/ዴታ ማከማቻና ማስተዳደሪያ ስልት።
ድንጋጌ (definition)
ያንድ ነገር ምንናማንነት ገለጻ። ለምሳሌ፥ የቃላት ትርጉም፤ ይህ ምዕላደ-ቃላት ሊያደርግ እንደሚሞክረው።
ጃቫ (Java)
በሰን ማይክሮሲሰትምስ (Sun Microsystems) የተፈጠረ ፕሮግራም መጻፊያ ቋንቋ። ባሁኑ ሰዓት ከፍተኛ ተወዳጅነት ያተረፈ። ፕሮግራም ለመጻፍ አመቺ የሆነ።
ገጽ መግለጫ ቋንቋ (page description language)
የጹሑፎች እንዲሁም የሥዕሎች አቀማመጥ መወሰኛ ቋንቋ፥ እንደ ሃቴማላ ያለው።
ግርጌ ማስታወሻ (footnote)

የገጾች የታችኛው ቦዶ ክፍል ኀዳግ ተብሎ ይጠራል። በዚህ ሥፍራ ገጹ ውስጥ ያለውን ጽሑፍ ለመደገፍ የሚጻፍ ማብራሪያ፥ ጥቅስ፥ ማስረጃ፥ አጣቃሽ ነገር።

ግራ ኧንግል ብራኬት (left angle bracket)

የላቲን ሆሄ (<)

ጠባየ-አንቀጽ (XML attribute)
ጠባየ-አንቀጽ፦ ያንድን አብይ አንቀጽ ጠባዮች ይደነግጋል።
ፊደል (alphabet)

ከሀ--ፐ፥ ከ0-9፥ የመሳሰለው።

ፋይል (file)

1ኛ ማንኛውም ወደ ኮምፕዩተሩ የሚገባና የሚወጣ ነገር፥ ዴታን ጨምሮ በፋይል ይጠናቀራል። ፋይል የራሱ የሆነ ስም፥ የይዘት አይነት፥ የተፈጠረበት ቀን፥ እንዲሁም መጠን አለው። ለምሳሌ፥ ኤለክትሮኒካዊ መልክቶች ከቦታ ቦታ የሚጓዙት በፋይል መልክ ተጠናቅረው ነው። ዲስኮች ላይ ይዘቶች የሚሰበሰቡት በፋይል ነው። ዌብ ላይ የምናያቸው ነገሮች በሙሉ የሚመጡት በፋይል መልክ ነው። ያለፋይል ምኑን ከምን!!! 2ኛ ፋይል ከታታ (save file)፦ ፋይልን ዲስክ ላይ መጻፍ፥ መቅርጽ፥ ወይም ማስቀመጥ። ይዘቱ ተቀይሮ ሜሞሪ ውስጥ ያለን ፋይል ወደ ዲስክ መጻፍ። 3ኛ ፋይል ግልበጣ (copy file)፦ ካንድ ዲሰክ ወደ ሌላ ፋይል መገልበጥ ወይም አንድን ፋይል በሌላ ስም መድገም። 4ኛ ፋይል ሽግግር (move file)፦ ካንድ የዲስክ ቦታ ፋይል መሠረዝና ወደ ሌላ ቦታ መጻፍ። 5ኛ ፋይል ሠረዛ (delete file)፦ ከዲስክ ላይ ፋይል ማንሳት፥ ማጥፋት፥ መደምሰስ።

ፎንት፥ ሥርዓተ-ፊደል (font)

1ኛ ፊደል፥ አኀዝ ፥ ሥርዓተ-ነጠብ፥ አይነተኛ ምልክቶችን ያቀፈ፤ 2ኛ አንድ አይነት መልክ፥ መጠን፥ ቀለም ያለው፤ 3ኛ ጹሑፎችን የሞኒተር ገጽታ ላይ ለማሳያት ወይም ወረቀት ላይ ለማተም የሚያስችል፤ 4ኛ የሆሄያትን መልክ በፎርሙላ የሚወክል።

ፕሮግራም (program)
ልዩ ልዩ ተገባራትን ማለትም የጹሑፎች፥ የዴታቤዝ፥ የሥዕል፥ የስፕርድሽትና ሌሎች ሥራዎችን ለማከናወን የሚያስችል፥ በፋይል መልክ የተጠናቀረ መመሪያ። ፕሮግራም፥ በጃቫ ወይም በመሳሰሉት ቋንቋዎች ይጻፋል።
ፕሮግራም መጻፊያ ቋንቋ (programming language)
ለኮምፕዩተሮችና ልዩ ልዩ መሣሪያዎች መመሪያ መጻፊያ ቋንቋ። ጃቫ (Java)፥ ሲ (C)፥ ሲ++ (C++) እንዲሉ።
ፓርሰር (parser)
የኤማላ ፓርሰሮች (parsers) ኆኅያትን አይጥሉም። ፓርሰሮች የኤማላ ሰነድ በልተው (ሸንሽነው) ለተጠቃሚው ፕሮግራም የሚያቀርቡ የኮምፕዩተር ፕሮግራሞች ናቸው። ለምሳሌ ፥ የመቃኛ ፕሮግራም አንድ የኤማላ ሰነድ ዌብ ገጽ ላይ ለማሳየት ፥ ይዘቱን መንጥሮ የሚያወጣለት የፓርሰሩ ፕሮግራም ነው። ስለዚህ ማንኛውንም ለአቅመ-ሥራ የደረሰ የኤማላ ሰነድ ለሥራ ስናሰመራ ፥ የመጀመሪያው ሂደት በፓርሰሩ በኩል ማለፍ ነው።
ፕሮግራም ጸሐፊ (program writer)
የፕሮግራም ቋንቋዎችን ተጠቅሞ ፕሮግራም የሚጽፍ፤ ሞያው ያደረገ።


...
smirmir@senamirmir.org
©Senamirmir Project, 2001