XML Overview in Amharic









XML Overview
Introduction
HTML Overview
XML Overview












  


ኤማላ (XML)

ኤማላ፠ (Extensible Markup Language) ፥ ከዕለት ወደ ዕለት ፥ የኢንተርነትን መልክአ-ምድር አየቀየረ ነው። እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ እንደማይሄድ ጉልህ ምልክቶች አሉ። ስለዚህ ለኤማላ ልባዊ ትኩረት ልንሰጥ ይገባ ይሆናል። በዚህ ክፍል ስለኤማላ ባጭሩ አብይ ነጥቦችን እናወሳለን ፦ የኤማላና ሃቴማላ ግንኙነት ፥ ኤማላ ሰነድ ፥ ሰነድ አይነት ደንጋጊ ፋይል ፥ ኤማላ ለኢትዮጵያ ቋንቋዎች ስላለው ድጋፍና የመሳሰሉት።

ኤማላና ሃቴማላ

  • ሁለቱም የኤስ/ጂ/ኤም/ኤል (SGML) ውላጅ ናቸው።
  • ኤማላ ፥ አዲስ ፟ይዘት መግለጫ ቋንቋ፠ መፍጠሪያ ወይም መደንገጊያ ነው። ሃቴማላ ግን ገጽ መግለጫ ቋንቋ ነው። በሃቴማላ ሰነድ እንጂ ሌላ ቋንቋ መፍጠር አይቻልም። እንደ ሃቴማላ ያለው ፟ቃለ-ምልክት ቋንቋ፠ ተብሎ ይጠቀሳል። በኤማላ ሃቴማላን መፍጠር ይቻላል ፤ በሃቴማላ ግን ምንም።
  • የኤማላ ሰነድና የሃቴማላ በደባልነት የሚኖሩበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል።
  • ኤማላ ሃቴማላን አይተካም ወይም ሃቴማላ ኤማላን አይተካም። ነገር ግን ኤማላ ሃቴማላን መፍጠር ይችላል።
  • የኤማላን ሕግ የጣሰ ሰነድ ሥነ ሥርዓተ-ቢስ ይሆናል። ሕጉን መከበር በሚጠብቁ አካሎች ዘንድ ተቀባይነት ያጣል። በሌላ በኩል ፥ የሃቴማላ ከሆነ ግን ስህተት ቢኖረውም ወይም ህግ ቢጥስም ፥ ዕድል አይነፈግም።
  • የኤማላ ቃለ-ምልክቶች ባለሰነድ-ሰራሽ ሲሆኑ ፥ የሃቴማላ ግን በW3C በቅድሚያ የተደነበዩ ናቸው። መቀየር ፥ መለወጥ ፥ ወይም መሻር አይቻልም።

ኤማላ ምሳሌ

አሁን የኤማላ ሰነድ ምን እንደሚመስል በተግባር ለማየት እንሞክራለን። ባለፈው ክፍል የተጠቀምነውን ምሳሌ እዚህ በማምጣት ፥ ወደ ኤማላ-ሰነድ እንቀይረዋለን።

  ምስል 1.1
 

<?xml version="1.0">
<!DOCTYPE country SYSTEM "./rivers.dtd">
 <rivers>
   <river>
     <name>Nile</name>
     <length>6696km<length>
  </river>

  <river>
    <name>Awash</name>
    <length>700km<length>
  </river>

  <river>
    <name>Tekeze</name>
    <length>752km<length>
  </river>

  <river>
    <name>Omo</name>
    <length>644km<length>
  </river>
</rivers>
   

ከሁለቱ የመጀመሪያ መስመሮች ፦ አንደኛው የሰነዱን አይነት ሲያበስር ሁለተኛው ደግሞ ክዳኖቹ የተሰየሙበትን ፋይል ስም።

ከመጀመሪያ ሁለት መስመሮች ውጭ የተጠቀምናቸው ቃለ-ምልክቶች በሙሉ ፟ባለሰነድ-ሠራሽ፠ ናቸው። ሥየማቸውና ያሰካክ መዋቅራቸው ፥ ስሙ ፟rivers.dtd፠ በተባለው ፋይል ውስጥ ይገኛል። ስማቸውን መፍጠር ፥ መቀየር ፥ ርባታቸውን መቀነስ ወይም መጨመር ፥ እንዲሁም መዋቅራቸውን መለወጥ እንችላለን። ለዚህ ነው ፥ ቃለ-ምልክቶችን ባለሰነድ-ሠራሽ የምንላቸው። ወሰን የሌለው ኃይል ያጐናጽፉናልና።

የቃለ-ምልክቶቹ አሰካክ ፥ ሥርዓትና ቅደም ተከተል ስላለው ፥ በጥንቃቄ ያን ማክበር ግዴታ ነው። በምሳሌያችን ፥ የ<rivers>> ቃለ-ምልክት በውስጡ የ<river> ቃለ-ምልክት ያቅፋል። የ<river> ቃለ-ምልክት ደግሞ በተራው የ<name> እና <length> ያዝላል። ይዘት ለማቀፍ የሚፈቀድላቸው ቃለ-ምልክቶች <name> እና <length> ናቸው። የተሰየሙት ሥራ ያ ስለሆነ። ይኸን ያሰካክ ሥርዓት ብናዛባ ፥ ሰነዳችን የተሟላ አይሆንም። ሳናውቅ ስህተት ብንሠራም ፥ ሰነዱ እንደጐደሎ ይቆጠራል።

እያንዳንዱ ከፋች ቃለ-ምልክት በወገኑ የግድ መገጠም አለበት። ለምሳሌ <rivers></rivers> ቃለ-ምልክት። የሌሎቹም እንደዚሁ። ግድፈት ያዘሉ ቃለ-ምልክቶች ፥ ሰነድን ለጥፋት ያበቃሉ። ቃለ-ምልክቶቹ ፥ በሰነድ-አይነት-ደንጋጊው ፋይል ውስጥ ወይም እዚህ በቅድሚያ የተሠየሙ መሆን አለባቸው። በደፈና አነጋገር ፥ ላፈጣጠራቸው ፥ ላጠቃቀማቸው ፥ እንዲሁም ላተረጓጐማቸው ሙሉ ኃላፊ እኛ ነን። ምንም እንኳን እዚህ ባንነጋገርበትም ፥ የrivers.dtd ፋይል ይዘት እንደሚከተለው ነው።

  ምስል 1.2
 
<!ELEMENT rivers (river)?>
<!ELEMENT river (name, length)>
<!ELEMENT name (#PCDATA)>
<!ELEMENT length (#PCDATA)>
   

ቢያንስ አንድ የኤማላ ፟ሥራ-በቅ፠ (Application) ፥ አንድ ወይም የተሳሰሩ ካንድ በላይ ሰነድ-አይነት-ደንጋጊዎች ፥ እንዲሁም አንድ ወይም የተሳሰሩ ካንድ በላይ ኤማላ ሰነዶች ያዝላል።

ኤማላና የኢትዮጵያ ቋንቋዎች

እንበል ፥ በራሳችን ቋንቋ የኤማላ ሰነድ ማዘጋጀት እንፈልጋለን! የሰነዳችን ይዘት ባማርኛ ከተጻፈ ፥ ሁሉንም አማርኛ ባማርኛ ብናደርገው ላዘጋጁም እንዲሁም ለተጠቃሚው ያመቻል። ስለዚህ ፥ ያማርኛ ኤማላ ሰነድ እነሆ፦

  ምስል 1.3
 
<?xml version="1.0">
<!DOCTYPE country SYSTEM "./rivers.dtd">
 <ወንዞች>

   <ወንዝ>
     <ሰም>ዐባይ</ስም>
     <ርዝመት>6696ኪሜ</ርዝመት>
   </ወንዝ>

   <ወንዝ>
    <ሰም>አዋሽ</ሰም>
    <ርዝመት>700ኪሜ</ርዝመት>
   </ወንዝ>

   <ወንዝ>
    <ሰም>ተከዜ</ሰም>
    <ርዝመት>752ኪሜ</ርዝመት>
   </ወንዝ>

   <ወንዝ>
    <ሰም>ኦሞ</ሰም>
    <ርዝመት>644ኪሜ</ርዝመት>
   </ወንዝ>

</ወንዞች>
   

ይህ ምሳሌ ፥ ከቋንቋ በስተቀር ፥ በሁለመናው ከዚህ በፊት ካያነው አይለይም። በግል ቋንቋ ሲጻፍ ፥ ለማንበብና ላጠቃቀም ይቀላል። ዓላማችን መፍትሄ መሻት ነውና። ሥራችን የተሟላ እንዲሆን ፥ ሰነድ-አይነት-ደንጋጊ ፋይሉን እናሻሽል።

  ምሳሌ 1.4
 
<!ELEMENT ወንዞች (ወንዝ)?>
<!ELEMENT ወንዝ (ስም, ርዝመት)>
<!ELEMENT ስም (#PCDATA)>
<!ELEMENT ርዝመት (#PCDATA)>
   

እንደኛ ከሆነ ፥ ሥራችንን በዚህ ደረጃ አጠናቀናል። ሰነዳችን ሥራ-ብቁ ነው። ይሁን እንጂ ፥ ምንም እንኳን ፥ ይህ ሥራችን በጐ መስሎ ቢታይም ፥ ለኤማላ 1.0 ከፍተኛ ስህተት አለው። ኤማላ 1.0 በኢትዮጵያ ፊደል የተጻፉ ቃለ-ምልክቶች ማለትም አብይ-አንቀጾች ፥ ጠባየ-አንቀጾች ፥ እንዲሁም ሰያሚ-አንቀጾች በጭራሽ አይቀበልም። ስለሆነም ፥ ይህ ሰነድ ተቀባይነት ያጣል። ለሥራ ብቃት የለህም ይባላል። ርባነቢስ እንዲሉ። አጥብቀን ማስተዋል ያለብን ነገር ቢኖር ፥ የይዘቱ ባማርኛ መጻፍ የችግሩ መንስኤ አለመሆኑን ነው። በዚህ ጉዳይ ፥ የኤማላ ጠብ ከይዘቱ ጋር አይደለም ፥ ከቃለ-ምልክቶቹ ፊደል እንጂ። በመዋቅር ረገድ ግን የተጣሰ ሕግ የለም።

ለመሆኑ ፥ ኤማላ 1.0 ለምን የኢትዮጵያን ፊደል አይቀበልም? መልሱ ከዩኒኮድ ታሪክ ጋር ይያያዛል። ኤማላ ቁጥር 1.0 የወጣው እአአ 1998 ነበረ። በጊዜው የነበረውን የዩኒኮድ ደንብ ቁጥር 2.0 በማያሻማ መንገድ ደገፈ። ከዛ በኋላ ፥ ዩኒኮድ 3.0 ሲወጣ ፥ የኢትዮጵያ ፊደልና ጥቂት ሌሎች ተቀባይነት አግኝተው ታተሙ። ኤማላ ግን ከዚህ አዲስ ሁኔታ ጋር ራሱን ስላለቀራረበ ፥ በዩኒኮድ 3.0 እና ከዛ በኋላ የወጡትን ፊደላት ሳይቀበል እንዳለ አለ።

በመሆኑም ፥ በኤማላ 1.0 ላይ የሚመኩ ፕሮግራሞች (XML applications) ፟ከዩኒኮድ 2.0፠ ውጭ በሆኑ ፊደላት የተጻፉ ቃለ-ምልክቶችን አንቀበልም ይላሉ። በይዘት ደረጃ ግን ችግር የለባቸውም። ቃለ-ምልክቻቸው ወይም መዋቅራቸው ተቀባይነት ያጡ ሰነዶች ፥ ሥነ ሥርዓት የጐደላቸው ሰነዶች ይሆናሉ።

ጭላንጭላዊ መፍትሄ

በቅርቡ ይህንና የመሳሰሉትን ችግሮች ለማስወገድ የቀረበ ውጥን አለ። ስሙ ፟ሰማያዊ እንጆሪ፠ (Blueberry) የተሰኘው ውጥን ፥ በዩኒኮድ 3.0 እና 3.1 የወጡትን ፊደላት በኤማላ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ይጠይቃል። ጉዳዩ ለውይይት ተከፍቶ ፥ ሃሳብ እየተሰነዘረበት ነው። ማንኛውም ሰው ፥ ሃሳብ የመስጠት መብቱ ሙሉ በሙሉ የተጠበቀ ስለሆነ ፥ አግባባዊ አስተያየት መሰንዘር ይበጃል። ውጥኑ በቂ ደጋፍ ካገኘ የማለፍ እድሉ ይጨምራል ፥ ካልሆነ የመውደቅ ዕጣ ይገጥመዋል። ስለዚህ ፥ ምን ማድረግ አለብን?

  1. በኤማላ ተፈላጊነት ላይ ሃሳብ መለዋወጥ ፥ ሥልጣኔውን በቅርብ መመርመር ፤
  2. ለምን የሰማያዊ እንጆሪ (Blueberry) ውጥን እንደተፈለገ ሁኔታውን ማጥናት ፤ ብሎም ብርቱ ድጋፍ መስጠት ፤
  3. በኤማላ ላይ የተመሰረቱ ልዩ ልዩ ውጥኖች ማውጣትና በተግባር ማዋል። ለምሳሌ ፦ መዝገበ ቃላት ፥ መጽሐፍት ፥ ጥንታዊ ቅርሳ-ቅርሶች ዝግብ ፥ የባህል መድኃኒቶች ዝግብና የመሳሰሉት።

ምንጮች



...
smirmir@senamirmir.org
©Senamirmir Project, 2001